የአልፋ ወዳጆች፣ አጋሮች፣ ቤተሰብና ዐባላት ሁላችሁ፣ ሠላምና ጤና ለእናንተና ለመላው ቤተሰባችሁ ከአልፋ ይድረሳችሁ ።
በአልፋ በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በእናንተ ያላሰለሰ ጥረትና ድጋፍ እንዲሁም በትጋት በሚሰሩ ሠራተኞች በታህሳስ ወር ሰፊና ትላልቅ ሥራዎች ተሰርተዋል። ዋና ዋናዎቹን እንደሚከተለው እናቀርባለን።
- አልፋ በአጠቃላይ 52 እናቶችንና 59 ልጆቻቸውን አገልግሎት ሲሰጥ፤ አዲስ በታህሳስ የተጨመሩና አገልግሎት ያገኙ 2 ሴቶችና 2 ልጆቻቸው ናቸው። እስከ አሁን በአራስ ቤት ሁለተናዊ አገልግሎት ያገኙ 26 ሴቶችና 28 ልጆቻቸው ናቸው። በአራስ ቤት 8 ሴቶችና 8 ልጆቸው ድጋፍ በማግኘት ላይ ይገኛሉ።
- የአልፋ ተጠቃሚዎች ራስ በማስቻል መርሀ- ግብር ተደራጅቶ በተለያዩ ስልጠናዎች፣ ገለፃና ምክር በመስጠት 2 የሚያህሉ ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ አሰማርቷል። በተለይም ላይፍ ጌት ራስ በማስቻል ድጋፍና ሥልጠና እንዲሁም የሁለንተናዊ እገዛ ስለተደረገልን ከልብ እናመሰግናለን ።
- የአራስ ቤት ተጠቃሚዎች የህይወት ተሞክሮ ሥልጠናና ትምህርት በተለያዩ ርዕሶችና ባለሙያዎች ተስጥቷል። እነዚህም በአመለካከት፣ በግንኙነት፣ በኑሮ ዘይቤ ለውጥ አምጥተዋል። በተጨማሪም ሣምንታዊ የስፖርት እንቅስቃሴ እንዲሁም የጋራ የምክክርና የውይይት ጊዜ ወቅቱን ጠብቆ ተደርጎል።
- የአልፋ ወዳጆች የተለያዩ በዓላትን ለማድረግ፣ አራሶችን ለመጎብኘት፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት፣ ወዳጆቻቸውንም ለማስጎብኘት በመምጣት በመገኘታቸው፣ በሙያቸው፣ በምክራቸው፣ በገንዘባቸውና በአብሮነታቸው ድጋፍ አድርገዋል።
- ጥር 27/2014 ዓ.ም የጌታችንና የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የአልፋ ወዳጆች፣ ቦርድ፣ የአራስ ቤት ግብር ኀይል ዐባላት፣ ሠራተኞች፣ እንግዶች ከአራስ ቤት ነዋሪዎች ጋር በደመቀ ሁኔታ አክብረዋል፣ ልጆቻችንም ሆነ ታዳሚዎች በዕለቱ በነበረው በዓል ደስታቸውን ገልፀዋል ።
- በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊንና ትውልደ ኢትዮጵያዊ በተደረገላቸው አገራዊ ጥሪ መሠረት “ኑና አራስ እንጠይቅ” የሚል በራሪ ፁሁፍ (flier) በማዘጋጀትና እንግዶችን በመጋበዝ ብዙ ሰዎች ጉብኝት አድርገዋል። ውጤታማም ነበር። ይህ የጥሪ ግብዣ የሚቀጥል ሲሆን በተዘጋጀው የመርሀ ግብር ሌሎችንም በመጋበዝ “አራሶችን” እንዲጎበኙ እንድታደርጉ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
- የነፋስ ሰልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚ የልደት በዓልን ምክንያት በማድረግ የአራስ ቤት ነዋሪዎችን በመጎብኘት የአምስት በግ ስጦታ አቅርበውልናል፣ በዓሉንም በደስታ አሳልፈዋል። ስለተደረገልን ስጦታ በተጠቃሚዎች ሥም ከልብ እናመሠግናለን ።
- የአልፋ ዓባልነት ለጉብኝት የመጡና በእናንተ በኩል ስለ አልፋ የሰሙ ቅፁን በመሙላት፣ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ዐባል የሆነችሁና ወደ እዚህ የቴሌግራም ቻናል የተቀላቀላችሁ እንኳን ደህና መጣችሁ እያልን፣ አሁንም በዚህ በጎ ተግባር ሊሰማሩ የሚችሉ ወዳጆችን ዐባል እንዲሆኑ እንድታበረቷቷቸው ጥሪ እናቀርባለን።
- የአልፋ የበጀት ዓመት ከጥር እስከ ታህሳስ በመሆኑ ነባር ዐባለት ዐባልነታችሁን እንደተለመደው እንድታድሱ፣ መረጃ ለማግኘት ከፈለጋችሁ በስልክ፣ በኢሜል እንዲሁም በፌስቡክና በቴሌግራም መጠየቅ ይቻላል።
- የአልፋ ቦርድ፣ ግብረ ኃይሎችና ኮማቴዎች የተሰጣቸውን ኃላፊነት በመደበኛና አስቸኳይ ስብሰባ እየተገናኙ የሚያከናውኑ ሲሆን አፈጻጸሙንም በየጊዜው ይከታተላሉ።
- እኤአ ከጥር ጀምሮ እሰከ በጀት መጨረሻ ድረስ የሚሰሩ ሥራዎች በመታቀድ ላይ ሲገኙ፣ በህጉ መሠረት ለመንግስት አካላትና የሦስትዮሽ የሥራ ስምምነት ከተደረገላቸው አጋር መሥሪያ ቤቶች የሚቀርቡ ሪፖርቶች፣ ዕቅዶች፣ በውጪ የሒሳብ መርማሪ የተሰራ የኦዲት ሪፖርት ዝግጅቶች ተጀምረዋል፣ በቅርቡም ለሚመለከተው አካላት ይቀርባል።
በማጠቃለያ ሥራዎቻችን ለመከወን የሚያስፈልገንን ሐብታት የሰጠን እግዚአብሔርን እያመሰገንን፣ ሁልጊዜ በሁለተናችሁ አጠገባችን በመቆምና አስፈላጊውን ድጋፍ ላደረጋችሁልን የአልፋ ወዳጆች በፋውንዴሽኑና በተጠቃማዎች ሥም ከልብ እናመሠግናለን ። በአዲሱ የበጀት ዓመትም የእናንተን የማያቋርጥ ድጋፍ ስለምንፈልግ አብራችሁን እንድትቆሙ ጥሪ እናቀርባለን ።
የአምላክ ልጆች ፋውንዴሽን-ጥር/2017 ዓ.ም