የአምላክ ልጆች ፋውንዴሽን አባላት፣ ወዳጆች፣ ቤተሰብና አጋሮች ሁሉ ሠላም ለእናንተና ለወዳጆቻችሁ ይሁን።
ፋውንዴሽናችን በእግዚአብሔር ምህረትና በሁለተናቸው በተሰጡ ወዳጆችና አባላት ባደረጉት ያልተቋረጠ ልግስና፣ በጎፈቃደኞች ከሥራው ጋራ በመተባበራቸው፣ በትጋት ሥራቸውን በሚሰሩ ሠራተኞች ብርቱ ሥራዎች ተሰርተዋል፣ ዋና ዋናዎቹን እንደሚከተለው እናቀርባለን ።
- በአራስ ቤት አገልግሎት ከጅማሮ ድጋፍ የተደረገላቸው ተጠቃሚ ሴቶች 47 ልጆቻቸው 49 ናቸው። በጥቅምት ወር አዲስ አገልግሎት ያገኙ 3 እናቶችና 3 ልጆቻቸው ሲሆኑ 3 የሚያህሉ ከእነ ጨቅላ ልጆቻቸው ወደ አራስ ቤት ገብተው ተገቢውን አገልግሎት በማግኘት ላይ ይገኛሉ ። በአራስ ቤት በዚህ ወቅት 9 እናቶችና 9 ልጆቻቸው ሁለተናዊ አገልግሎት እየተሰጣቸው ይገኛል።
- በጥቅምት ወር ራስ በማስቻል ሥራ በመሰማራት ሥራ የጀመሩ አሉ። አልፋ አስፈላጊውን የገንዘብ፣ የቁሳቁስ፣ የምግብ ፍጆታ በማገዝ ጥረት አድርጎል። ከእዚህ በተጨማሪም የሥራ ትስስር በማድረግ ሆፕ ፎር ኮራህ ከሚባል ግብረሰናይ ድርጅት ጋራ ለአምስት ለሚያህሉ የአልፋ ተጠቃሚዎች ራስ በማስቻል ሥልጠናና ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል። ላይፍ ጌትና ሆፕ ፎር ኮራህ ግብረሰናይ ድርጅቶች በአልፋና በተጠቃሚዎቹ ሥም እናመሠግናለን ። ትልቁን ሸክማችንን ተጋርተውልናል። ከእዚህ በተጨማሪ ከአራስ ቤት ውጪ ድጋፍ የሚደረግላቸው ሁለት ሴቶች ተጨማሪ እገዛ ተደርጎላቸዋል።
- በአራስ ቤት ነዋሪ የሆኑ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ትምህርት እየተሰጠ ሲሆን በተለይም በዚህ ወር ስለ አእምሮ መታወክ ምክንያቶች፣ የመውጫው መንገድ፣ እንዴት አእምሯችን ከጉዳት እንጠብቀው? በሚሉ ርዕስ ትምህርት ተካሂዷል ። ተጠቃሚዎችም ደስተኞች ነበሩ። ከእዚህ በተጨማሪ በሰፌትና በመሳሰሉት የሙያ ልምምድና ማስተማር ተደርጎል።
- አንድ የአራስ ቤት ነዋሪ እናት ከወላጆቿ ጋራ በአገር ባህል መሠረት አስታራቂ ሽማግሌዎችን በመያዝ ዕርቅ እንዲደረግ፣ ቤተሰቦቿም ወደ አገራቸው ይዘዋት እንዲሄዱ ተደርጎል። በዚህ ድጋፍ ያደረጉልንን አባት ከልብ እናመሰግናለን ።
- የአልፋ ልዩ ዓመታዊ ክብረ በዓል ጥቅምት 27/2014 ዓ.ም ከ100 ሰው በላይ በመገኘት በደመቀና ደስ በሚያሰኝ ስሜት ተጠናቋል። ከ49 በላይ የሆኑ አዳዲስ አባላት ተጨምረዋል፣ ከ38 በላይ የሚሆኑ የቃል ኪዳን ቅፅ በመሙላት ተስፋ ሰጥተዋል፣ ብዙዎቹም የገቡትን ገንዘብ ቃል በጥሬ ገንዘብና በባንክ ገቢ አድርገዋል ። በዚህ አጋጣሚ ጥሪያችን ተቀብላችሁ የመጣችሁ ሁሉ ከልብ እናመሰግናለን ። በተለያዩ ምክንያቶች ያልተገኛችሁ የቢሮ ሠራተኞችን ብታገኙ በዕለቱ የቀረቡትንና የሚጠበቅባችሁን ይነግሯችኃል።
- በአራስ ቤት ተጠቃሚ ከሆኑ ልጆች መካከል አንድ ጨቅላ ሲመጣ በጉዳት ላይ የነበረ በመሆኑ አለርት ሆስፒታል በማስተኛት የህክምና ክትትል እየተደረገለት ሲሆን የአይሲው ህክምና ጨርሶ መኝታ ክፍል ተሰጥቶት ከአስር ቀናት በላይ በመታከም ላይ ይገኛል። እግዚአብሔር ከሚያስደነግጥ አደጋ ስለታደገን እናመሰግናለን ። የአለርት ሆስፒታል የህክምና ባለሙያዎችም ልጃችንን ለማዳን ስላደረጉልን ርብርቦሽ በአልፋ ሥም እናመሰግናለን ።
- በአራስ ቤት የሚገኙ ጭቅላ ህፃናትና ወላጆቻቸው ተገቢው የህክምና ክትትል ይደረግላቸዋል፣ ክትባትም ወደ ጤና ጣቢያ በመውሰድ በወቅቱ ተሰጥቷቸዋል ።
- የአልፋ ቦርድ፣ ግብረ ኀይሎችና የአልፋ ልዩ ክብረ በዓል አዘጋጅ ኮማቴ በመደበኛ ስብሰባዎቻቸው በመገናኘት ለሥራው የሚያስፈልጉ ተግባራትን ፈፅመዋል።
- የአልፋ የበጀት ዓመት ከጥር-ታህሳስ ያሉት ጊዜያት ናቸው። በዚህ ወቅትም ሰፋፊ ስራዎች ለመሥራት ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል። ከስራዎቹ አንዱ ዐባላት አዲሱ ዓመት ከመጀመሩ በፊት ዐባልነታቸውን እንዲያድሱ ማሳሰብ ነው። ስለሆነም በእነዚህ አንድ ወራት ውስጥ አባልነታችሁን እንድታድሱ በአክብሮት እየጠየቅን፣ የአባልነት ቅፁን ሞልቶ በቴሌግራም ወይም በአካል መስጠት ይቻላል።
በመጨረሻም በእነዚህ ሰፋፊ ስራዎች በመሥራት መከናወን ያደረገልንን እግዚአብሔርን እናመሠግናለን ። በተጨማሪም እናንተ የአልፋ ወዳጆችና ቤተሰቦች ሁሉ በሚቻላችሁ ሁሉ ከእኛ ጋራ በመቆም ውጤታማ ስላደረጋችሁን ከልብ እናመሰግናለን ። በቀጣዩም ሥራችን እንደከዚህ ቀደሙ እጃችንን በመያዝ ከእኛ ጋራ እንድትቆሙ በአክብሮት ጥሪ እናቀርባለን ።
የአምላክ ልጆች ፋውንዴሽን-ኅዳር 7/2014 ዓ.ም