የአምላክ ልጆች ፋውንዴሽን ዐባላት፣ ወዳጆችና ቤተሰብ በሙሉ ፣ ሠላምና ጤና ለእናንተና ለመላው ቤተሰቦቻችሁ ይሁን።
አልፋ በእግዚአብሔር ቸርነቱ ብዛት፣ ሥራውን በሁለተናቸው ድጋፍ ባደረጉልን ወዳጆችና ዐባላት፣
የሚሠሩትን በማወቅ በትጋት በሚያከናውኑ ሠራተኞች አያሌ ሥራዎች ተከናውነዋል፣ አንኳሮችን እናቀርባለን።
- የአልፋን አገልገሎት በቀጥታ ድጋፍ ያገኙ 48 ወላድ ሴቶችና 50 ልጆቻቸው ናቸው። በአራስ ቤት ነዋሪ በዚህ ወር የነበሩ 9 እናቶችና ልጆቻቸው ሲሆኑ አንድ እናት የስድስት ወራት የመታረሻ ጊዜዎን ጨርሳ በቤት ሠራተኝነት ለማገልገል ሥራን ተገኝቶላት ተሰማርታለች። በተጨማሪም አንድ አራስ ከጨቅላ ህፃኗ በዚህ ወር ወደ አራስ ቤት ሁለተናዊ አገልግሎት ለማግኘት ገብታለች።
- የአራስ ቤት ተጠቃሚዎች በተለያዩ ርዕሳን በተጠናከረ መልኩ ለእነርሱ ወቅታዊና ተገቢ፣ ሙያን ያማከለ ትምህርት የተሰጠ ሲሆን የስፖርት እንቅስቃሴም አድርገዋል። ከተሰጡት ትምህርቶች የአእምሮ ጤንነት አጠባበቅ፣ የችግር ምንነትና የአፈታት ዘዴ፣ የእናትና የልጅ ትስስር ዋና ዋና ናቸው። በተጨማሪም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይትና ምክክር አድርገዋል ።በጣም ጠቃሚ ነበር።
- የአምላክ ልጆች ፋውንዴሽን ተጠቃሚዎች ለሁላቸውም በስማቸው የባንክ ደብተር የተከፈተላቸው ሲሆን እናትዬውና ልጃቸው በቂ የህክምና አገልግሎት በሚያስፈልጋቸው ጊዜ እንዲያገኙ የጤና መድህን ሽፋን ለዘጠኝ ሴቶችና ልጆቻቸው ክፍያውን አልፋ በመፈፀም የጤና መድህን ዐባል ሆነዋል። ይህም ትልቅ እምርታ ሆኖልናል።
- ጥቅምት 27/2014 ዓ.ም በነበረው ልዩ የአልፋ ቀን ተሳታፊ የሆኑ ወዳጆች ብዙዎቻቸው የዐባልነት ቅፅ በመሙላትና ክፍያቸውን በመፈፀም ዐባል ሆነዋል።
አዲስ ዐባል የሆኑትን ሁሉ በአልፋ ሥም እንኳን መጣችሁልን እንላለን። ሰፊ ሥራ አለና በአቅማችሁ ሁሉ መሳተፍ እንድትችሉ፣ በስልካችን ልታገኙን ትችላላችሁ፣ በየጊዜው በምናቀርባቸው ሪፖርቶችና አስተያየቶችም መሳተፍ ይቻላል። - በአራስ ቤት ውስጥ የተለየ ክስተት የነበረበት ወቅት ነበር። ሊዲያ ዳዊት ዕድሜዋ 16 የሆነች ወጣት የልደት በዓሏን ወዳጆቿ፣ ቤተሰቦቿ፣ ጥሪ የተደረገላቸው ጓደኞቿ በተገኙበት ከአራስ ቤት ሴቶችና ልጆቻቸው ጋራ በመሆን በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል። ትልቅ ደስታ፣ ልዩ የሐሴት ድባብና የኅብረት ጊዜ ለልጆቻችንም መነቃቃት የነበረበት ወቅት መሆኑን ተገንዝበናል። ተሳታፊዎችም ስለ አልፋ አጀማመርና ሥራ ገለጻ ተደርጎላቸዋል፣ የሥራ እንቅሰቃሴ ጎብኝተዋል። የዐባልነት ቅፅ በመሙላትም ዐባል ሆነዋል። ሊዲያና ቤተሰቦችሽ ከልብ እናመሠግናለን ። አስተማሪነት ያለው እርምጃ ወሰደሻል፣ ሁላችንም ደስብሎናል።
ለወደፊቱም የአልፋ ዐባላት የተለያዩ በዓሎችን ለማድረግ ከፈለጋችሁ ቀደም ብላችሁ ብታሳውቁን እናንተንም ሆነ የአራስ ቤት ተጠቃሚዎችንም ጭምር ሐሴት ሊያስደርግ በሚችል መልኩ የምናዘጋጅ መሆኑን እናሳውቃለን ። - የአልፋ የበጀት ዓመት ከጥር እስከ ታህሳስ መሆኑ ይታወቃል ። አሁን ያለንበት ወር የዓመቱ የበጀት መዝጊያ ስለሆነ የታቀዱና ያልተጠናቀቁ ሥራዎች የትኩረት አቅጣጫ በማድረግ እየተሰሩ ይገኛሉ።
አንዱ የበጀት ዓመቱ ከመጠናቀቁ በፊት ዐባል የነበሩ ወዳጆች ለሚቀጥለው የበጀት ዓመት ለሥራ የሚያስፈልገውን ሐብታት ለማሰባሰብ ዐባልነታቸውን እንዲያድሱ ማሳሰብ ነው።
ስለዚህ የአልፋ ቤተሰቦች ዐባልነታችሁን እንድታድሱ በአክብሮት እንጠይቃለን። ከሥራውም ጋር አብራችሁን ስለቆማችሁ በተጠቃሚዎቹ ሥም በድጋሚ እናመሠግናለን ። - የአልፋ ቦርድ፣ ግብረ ኀይሎችና ኮሚቴዎች የተመደቡበትን ሥራ እንደ ወትሮው እየተገናኙ የሚመለከታቸውን በትጋትና በታማኝነት እየሰሩ ይገኛሉ።
በመጨረሻ በእነዚህ ሁሉ የሥራ ክንውን የረዳንን አምላካችንን እናመሠግናለን ። እናንተም የአልፋ ወዳጆች በምታደርጉልን ያላሰለሰ ድጋፍና መሰጠት ሥራዎቻችን ተከናውኖ ብዙ ወላድ ሴቶችና ጨቅላ ህፃናትን መደገፍ ችለናልና ከልብ እናመሠግናለን ። ይህ ችሮታችሁና አብሮነታችሁ በቀጣይ ሥራም እንዲዘልቅ ጥሪያችንን በተጠቃሚዎቹ ሥም እናቀርባለን።
የአምላክ ልጆች ፋውንዴሽን-ታህሳስ 1/2014