የአምላክ ልጆች ፋውንዴሽን (የአልፋ) በሲቭል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ የህግ ሰውነት አገኝቶ ልባቸው ለበጎ ሥራ በተዘጋጀ ሰዎች ድጋፍ ሰፊ ራዕይን አንግቦ እና ትኩረቱን ችግረኛና መጠጊያ የሌላቸዉ እናቶችና ጨቅላ ሕጻናቶቻቸዉ ላይ በማድረግ የከተማችን ማህበራዊ ቀውስ ለመቅረፍ በሚደረገዉ ጥረት ዉስጥ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል::ፋዉንዴሸኑ ባለፉት ሦስት ዓመታት ተኩል በ164 ችግረኛና መጠጊያ የሌላቸዉን እናቶችና 167 ጨቅላ ሕጻናቶቻቸዉ በጠቅላላ 331 ድጋፍ የሚሹ ኢትዮጵያዊያንን ማገልገል ችሏል፡፡
ከየአልፋ የአልግሎት ምሰሶዎች ዋና የሆነዉ የአራስ ቤት አገልግሎት ትኩረቱ በመንግስት ጤና ተቋማት ለሚወልዱ የድሃ ድሃ እናቶች የአልባሳትና የንጽህና ቁሳቁስ ለጤና ጣቢያዎች በማቅረብ መደገፍ፣ የሚያርፉበት መጠለያ ላላቸው ችግረኛ ወላድ እናቶች ደግሞ ባሉበት ቦታ የምግብ አቅርቦት በማድረስ ማረስ ሲሆን ምንም መጠለያ የሌላቸውንና ወደ ጎዳና ሊወጡ ያሉ ወላድ እናቶችንና ጨቅላ ህጻናቶቻቸውን ደግሞ ወደ አራስ ቤት ማዕከሉ በማስገባት ለስድስት ወራት መንከባከብና ራሳቸውን እንዲችሉ ማገዝ ነው፡፡ በቆይታቸውም ምክርና ልዩ ልዩ የሙያ ስልጠና በመስጠት እንዲቋቋሙ ያደርጋል፡፡ የአራስ ቤት አገልግሎታችንንም ማልበስ ፣ ማረስ፣ ማሰልጠን እና ማቋቋም በሚል ዋና ዋና የስራ ሂደቶች ከፍለን እያገለገልን እንገኛለን፡፡
ፋዉንዴሸኑ አየሰጠ ያለዉ ችግረኛና መጠለያ የሌላቸዉን እናቶችና ጨቅላ ሕጻናቶቻቸዉ ላይ ያተኮረ አገልግሎት በላቀ ደረጃ ለማስቀጠልና ሥራውን ለማሕበረሰቡ ለማስተዋወቅ እንዲሁም ደጋፊዋችን ለማግኘትና ድጋፍ ለማሰባሰብ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወራዳ 02 በስተጀርባ በሚገኘው የፋዉንዴሸኑ አራስ ቤት ከሚያዚያ 18-20/2016 ዓ.ም ባዛር አዘጋጅቷል::
ስለዚህ ሚያዚያ 18 ቀን 2016 ዓ.ም ከጧቱ 4:00 ጀምሮ በሚካሄደዉ የባዛሩ መክፈቻ ስነሥርዓት ላይ እንድትገኙልን በትልቅ አከብሮት እንጋብዛለን።
አራስ እናት ጨቅላ ህጻኗን ይዛ ወደ ጎዳና እንዳትወጣ በጋራ እንታደግ!