የአምላክ ልጆች ፋውንዴሽን የየካቲት 2014 ዓ.ም የሥራ እንቅስቃሴ ።

0 Comment | 1:59 pm|


Categories:

የአልፋ ወዳጆች፣ ቤተሰቦች፣ ዐባላትና አጋሮች ለሁላችሁም የአልፋ ጽ/ቤት ሠላምታ ይድረሳችሁ።
አልፋ በእግዚአብሔር ዕርዳታ፣ በእናንተ ያልተቆጠብ ድጋፍ፣ የተለያዩ ግብረ ኀይሎችና ኮሚቴዎች ጥረት፣ የበጎ ፈቃድ ድጋፍ ሰጪዎች መሰጠት፣ ሥራውን በትጋት በሚያከናውኑ ሰራተኞች አማካይነት ብዙ ሥራ ተሰርቷል፣ ለችግር የተጋለጡ ወላድ ሴቶችና ጨቅላ ልጆቻቸውን አሳርፏል። ስለዚህ በሁሉ የረዳንን እግዚአብሔርን እያመሰገንን፣ የእናንተም የላቀ ተሳትፎን አድናቆት ልንሰጥ እንወዳለን። በእነዚህ አንድ ወራት የተሰሩ ዋና ዋና ሥራዎች እንደሚከተለው እናቀርባለን ።

  • አልፋ ሥራውን በይፋ ከጀመረ አንስቶ 62 ለሚያህሉ ወላድ ሴቶችንና 70 ልጆቻቸው ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፣ በአራስ ቤት በአጠቃላይ ገብተው ተጠቃሚ የሆኑ 30 ሴቶችና 32 ልጆቻቸው ናቸው።
    በየካቲት ወር 2 ሴቶች ከእነ ልጆቻቸው አዲስ የገቡ ሲሆን አስፈላጊው ድጋፍ ተደርጎላቸው አራስ ቤትን ለቀው የወጡ 3 ሴቶችና ልጆቻቸው ናቸው።
    አሁን በአራስ ቤት ተጠቃሚ ሆነው የሚገለገሉ 10 ሴቶችና ልጆቻቸው ናቸው።
  • በየካቲት ወር አስፈላጊውን ሥልጠናና ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደ ማቋቋሚያ የገቡ 11 ናቸው። በቢሮም በኩል ጉብኝትና ክትትል ይደረግላቸዋል።
    እስከ አሁን በማቋቋም ድጋፍ ከሚያደርጉ ድርጅቶች ጋራ የተቋቋሙ 11 ሲሆን ከቤተሰባቸው ጋራ በመታረቅ የተቀላቀሉ 5 ናቸው።
  • 10 ለሚያህሉ የፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች የንግድ ክህሎት ስልጠና ተሰጥቷቸው፣ ራሳቸውን ለሥራ እንዲያዘጋጁ ተደርጎል።
  • በአራስ ቤት ለሚገኙ ተጠቃሚዎች የተለያዩ ክህሎቶቻቸውንና አቅማቸውን ለማሳደግ ቢሮው በሚያዘጋጀው የስልጠናና የትምህርት መርሀ ግብር ተሰጥቷቸዋል። እነርሱም “የልጅ መመገብ ምንነትና ስለ ጡት ማጥባት” በዶ/ር ኤልሳቤጥ ቀርቦላቸዋል። ከእዚህ በተጨማሪ የአፍ ንፅህና አጠባበቅ እና በሌሎችም ርዕሳነ ጉዳዮች ላይ ትምህርት ቀርቦላቸዋል፣ ፍሬውም አመርቂና ለውጥ አምጥቷል። ዶ/ር ኤልሳቤጥን እናመሰግናለን።
  • የአራስ ቤት ተጠቃሚ ሴቶችና ልጆቻቸው አስፈላጊው የመኝታ፣ የአልባሳት፣ የተመጣጠነ ምግብ፣ የህክምና ክትትል፣ ክትባት፣ የንፅህና አጠባበቅ፣ የምክር አገልግሎት ተደርጎላቸዋል።
    በተጨማሪም እናቶችንና ልጆቻቸውን በህክምና ባለሙያ አራስ ቤት ድረስ ባለሙያ በማምጣት በዶ/ር ደበላ ጫሊ ህክምና ተደርጎላቸዋል ፣ የህክምና ሪፖርቱም ለቢሮ በመላክ ክትትል እየተደረገበት ይገኛል። ሐኪሙን ስለ በጎ ፈቃድ አገልግሎታቸው እናመሠግናለን ።
  • እኤአ የ2021 ዓ.ም የሒሳብ ምርመራ በውጪ ኦዲተር ተደርጎ፣ ተገቢውን የሥራ ሪፖርት ተጋጅቶ፣ እኤአ የ2022 ዓ.ም ዕቅድና በጀት ተሰርቶ በደንቡ መሠረት ቦርዱ አይቶ ካፀደቀ በኃላ ለሲቭል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ባዘጋጀው የሪፖርት ማቅረቢያ ቅጽ መሠረት ሁሉንም መረጃዎችና ሰነዶች አስገብቷል።
  • የአራስ ቤት የሥራና የሒሳብ እንቅስቃሴ የሦስትዮሽ ፊርማ ከተደረገው የመንግስት መ/ቤት (የፋይናንስና ገንዘብ አስተዳደር እና ከማህበራዊና ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ) እኤአ እስከ ታህሳስ/2021 ያለውን ሪፖርት አስገብቷል።
  • የቤት ኪራይ አብዛኛው የአልፋ ወጪ መሆኑን የኦዲት ሪፖርቱ ያመለክታል። ይህንን ችግር ለመቅረፍ ለንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የቦታ ወይም የቤት ድጋፍ ለማግኘት ደብዳቤ አስገብቶ ቀጠሮ እንዲሰጠውና በጉዳዩ ላይ ለመመካከር እየተጠባበቀ ይገኛል ።
  • የአልፋ ወዳጆች “ኑ እራስን እንጠይቅ” በማለት ብዙ ወዳጆቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውን በማምጣት ልጆቻችንን ጠይቀዋል፣ ገንፎ በልተዋል፣ ቡና ጠጥተዋል፣ ከአራሶችም ጋራ ተጫውተዋል፣ ተመካክረዋል ። በዚህም ጠያቂዎችም ተጠያቂዎችም፣ ቢሮው ሁሉ ሐሴት ማድረጋቸውን ስንገለሰፅ በታላቅ ደስታ ነው።
  • በተለያዩ ወቅት ወደ አራስ ቤት አራሶችንና ልጆቻቸውን ለመጠየቅ የመጡ እንግዶች እንዲሁም በተለያዩ እክል መምጣት ያልቻሉ ወዳጆች የገንዘብ፣ የአልባሳት፣ የንፅህና መጠበቂያ፣ የምግብ ግብዓት፣ የተለያዩ የመገልገያ ዕቃዎች ድጋፍ አድርገዋል። በዚህ ሁሉ የተሳተፋትን ከልብ እናመሰግናለን ።
  • የአልፋ ዐባላት ዓመታዊ የዐባልነት ድጋፋቸውን በመክፈል ዐባልነታቸውን ዐድሰዋል።
  • የአልፋ ቦርድ ከገንዘብና ዐባላት አሰባሳቢ ግብረ ኀይል በቀረበለት “የፋሲካ ባዛር” ዝግጅት ዝርዝሩን በመቀበል ሥራው እንዲፈፀም ወስኗል። ኮሚቴውም “የፋሲካ ባዛር” የተለያዩ ትምህርታዊ፣ ቤተሰብን ያማከለ ባዛር በኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበር ኮንፈደረሽን ግቢ ሚያዚያ 7-9/2014 ዓ.ም(ዓርብ፣ቅዳሜና እሁድ ቀኑን ሙሉ) የተዘጋጀ ስለሆነ ከወዲሁ በአጀንዳዎቻችሁ እንድትመዘግቡ፣ ሰዎች እንዲሳተፉ ቅስቀሳ እንድታደርጉ፣ በተለያዩ ዝግጅት ውስጥ እንድትሳተፉ፣ የኮሚቴው ጥሪና ድጋፍ ሲቀርብላችሁ ምላሽ እንድትሰጡ በአክብሮት እንጠይቃለን።
  • የአምላክ ልጆች ፋውንዴሽን ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ከመደበኛ ሥራዎቹ በተጨማሪ እየተፈታተኑት ያሉ ተግዳሮት ተደቅኖበታል ። የእናንተ ምክርና ድጋፍም እንጠይቃለን።
    እነርሱም:-
    . የቤት ኪራይ መጨመር፣
    . አራስ ቤት የምንጠቀምበት ቦታ መጥበብ፣
    . የኑሮ ውድነት (የፍጆታ ዋጋ መናር)፣
    . የምንጠቀምበት የአራስ ቤት ግቢ ባለቤቶቹ ለሌላ ጉዳይ ለመጠቀም ማሰብ ናቸው።

በማጠቃለያ ሥራዎቻችን በአማረ ሁኔታ ስለተጠናቀቀልን፣ ድጋፍ የሚደረግላቸው ሴቶችና ልጆቻቸው አቅም በፈቀደ መሠረት አስፈላጊው ድጋፍ ስለተደረገላቸው ይህንንም እንድንሰራ ለረዳንን አምላካችን ክብርና ምስጋና ይድረሰው።
በድጋሚ ለዚህ አስፈላጊና ዋና ለሆነው ራዕይ ገንዘባቸውን፣ ሙያቸውን፣ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ቁሳቁሳቸውን፣ ትስስራቸውን (network) በአጠቃላይ ሁለተናቸውን የሰጡንን ሁሉ ከልብ በተጠቃሚዎች ሥም እናመሠግናለን። በቀጣዩም ወር የተለመደው ድጋፋችሁን በማድረግ የተጨነቁትን እናሳርፍ፣ የደከሙትን እናበርታ፣ አቅጣጫ የጠፋባቸውን መንገድ እንጠቁማቸው፣ ተባብረንና ያለንን ሸክፈን የምንችለውን እንድናደርግ የተለመደው እገዛችሁን በአክብሮት እንጠይቃለን።

የአምላክ ልጆች ፋውንዴሽን-የካቲት/2014 ዓ.ም

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *